ብሉይ ኪዳን    አዲስ ኪዳን   Hide Verse Numbers    Hide Chapter Numbers  
በመጀመሪያ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች።[1] የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን። ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይከማች፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ። መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን። ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ለምድር ብርሃን ይሰጡ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናት አደረገ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን አደረገ። እንዲሁም ከዋክብትን አደረገ። ለምድር ብርሃን እንዲሰጡ እነዚህን በሰማይ ጠፈር አኖራቸው። ይኸውም በቀንና በሌሊት እንዲሠለጥኑ፣ ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ። መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጡራን ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጡራንን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። መሸ፤ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ሕያዋን ፍጡራንን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር[2] ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን። የሰማያትና የምድር፣ በውስጣቸውም ያሉት ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።[3] እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት እንደዚህ ነበረ፤ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር የሜዳ ቡቃያ ገና በምድር[4] ላይ አልታየም፤ የሜዳ ተክልም ገና አልበቀለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በመሬት ላይ ገና ዝናብ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚያለማ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ውሃ[5] ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ። የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በሐዊላ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የፊሶን ወንዝ ነው። ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ[7] ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ[8] ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የግዮን ወንዝ ነው። ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተ ምሥራቅ የሚፈሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም)፣ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ። ስለዚህ አዳም[9] ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው። ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንት[10] ወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት[11] ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት[12] ትባል።” ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር። እባብ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” አላት። ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሎአል።” እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደምትሆኑ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ስለሚያውቅ ነው።” ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ። ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሔዋን ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው። አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ (ያህዌ)፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣ “ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤[13] አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል።” አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከእርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣ “ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች፤ ከቡቃያዋም ትበላለህ። ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን[15] ብሎ ጠራት። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም)፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሠይፍ ከዔድን በስተ ምሥራቅ አኖረ።[16] አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን[17] ወለደች፤ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቀረበ። አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎች መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስቲ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ”[18] አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። ከዚያም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው። ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ምንድ ነው ያደረግኸው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” ቃየንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤[19] ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር (ያህዌ) በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። ቃየንም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተ ምሥራቅ በምትገኝ ኖድ[20] በተባለች ምድር ተቀመጠ። ቃየን ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ሄኖክን ወለደች። ቃየን የቈረቈረውን ከተማ በልጁ ስም ሄኖክ ብሎ ጠራው። ሄኖክ ኢራድን ወለደ፤ ኢራድም መሑያኤልን፣ መሑያኤልም ማቱሣኤልን፣ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ጺላ ነበር። ዓዳ ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ከብት አርቢዎች አባት ነበረ። ወንድሙም ዩባል ይባላል፤ እርሱም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበረ። ሴላም ደግሞ ቱባልቃይን የተባለ ወንድ ልጅ ነበራት፤ እርሱም ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ[21] ነበር። የቱባልቃይን እኅት ናዕማ ትባል ነበር። ላሜሕ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “ዓዳና ጺላ ሆይ ስሙኝ፤ የላሜሕ ሚስቶች ሆይ አድምጡኝ፤ አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣ ጒልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤[22] ቃየንን የሚገድል ሰባት ጊዜ ቅጣት ካገኘው፣ የላሜሕ ገዳይማ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል።” አዳም እንደ ገና ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምትክ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ሴት[23] ብላ ጠራችው። ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም መጥራት[24] ጀመሩ። የአዳም የትውልድ ሐረግ እንደሚከተለው ነው፦ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሲፈጥረው በራሱ አምሳል አበጀው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸው፤ በተፈጠሩም ጊዜ “ሰው”[25] ብሎ ጠራቸው። አዳም፣ ዕድሜው 130 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እርሱን ራሱን የሚመስል ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው። ሴት ሄኖስን ከወለደ በኋላ አዳም 800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ሴት፣ ዕድሜው 105 ዓመት ሲሆን ሄኖስን ወለደ፤ ሴት ሄኖስን ከወለደ በኋላ 807 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ሴት በአጠቃላይ 912 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ሄኖስ፣ ዕድሜው 90 ዓመት በሆነ ጊዜ ቃይናንን ወለደ፤ ሄኖስ ቃይናንን ከወለደ በኋላ 815 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ሄኖስ በአጠቃላይ 905 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ቃይናን፣ ዕድሜው 70 ዓመት ሲሆን መላልኤልን ወለደ፤ ቃይናን መላልኤልን ከወለደ በኋላ 840 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ቃይናን በአጠቃላይ 910 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። መላልኤል፣ ዕድሜው 65 ዓመት በሆነ ጊዜ ያሬድን ወለደ፤ መላልኤል ያሬድን ከወለደ በኋላ 830 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። መላልኤል በአጠቃላይ 895 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ያሬድ፣ ዕድሜው 162 ዓመት ሲሆን ሄኖክን ወለደ፤ ያሬድ ሄኖክን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ያሬድ በአጠቃላይ 962 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ሄኖክ፣ ዕድሜው 65 ዓመት በሆነ ጊዜ ማቱሳላን ወለደ፤ ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ አካሄዱን ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጋር በማድረግ 300 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ሄኖክ በአጠቃላይ 365 ዓመት ኖረ፤ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጋር አደረገ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ስለ ወሰደውም አልተገኘም። ማቱሳላ፣ ዕድሜው 187 ዓመት ሲሆን ላሜሕን ወለደ፤ ማቱሳላ ላሜሕን ከወለደ በኋላ፣ 782 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ ማቱሳላ በአጠቃላይ 969 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ላሜሕ፣ ዕድሜው 182 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ ልጅ ወለደ። ስሙንም “እግዚአብሔር (አዶናይ) በረገማት ምድር ከልፋታችንና ከጒልበታችን ድካም ያሳርፈናል” ሲል ኖኅ[26] ብሎ ጠራው። ላሜሕ ኖኅን ከወለደ በኋላ፣ 595 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ላሜሕ በአጠቃላይ 777 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። ኖኅ ዕድሜው 500 ዓመት ሲሆን ሴምን፣ ካምንና ያፌትን ወለደ። ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ። እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “ሰው ሟች[27] ስለ ሆነ መንፈሴ እያዘነ[28] ከእርሱ ጋር ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው 120 ዓመት ይሆናል” አለ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ። ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ሞገስን አገኘ። የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጋር አደረገ። ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። ምድር በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ፤ እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በእርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። አንተ ግን በጎፈር[29] ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው። እንዲህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13.5 ሜትር ይሁን። ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤[30] ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። ካንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ። ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።” ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዳዘዘው አደረገ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። ከንጹሕ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት[31] ተባዕትና እንስት፣ 3 ንጹህ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት እንዲሁም ከወፎች ወገን ሁሉ ሰባት ተባዕትና ሰባት እንስት፣ በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋር ታስገባለህ። ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ።” ኖኅም እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የ600 ዓመት ሰው ነበር። ኖኅና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለመትረፍ ወደ መርከቧ ገቡ። ንጹሕ ከሆኑትና ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ጥንድ ጥንድ፣ ተባዕትና እንስት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ መርከቧ ገቡ። ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ። በዚያኑ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ አብረዋቸው ገቡ። የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከውጭ ዘጋበት። የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ። በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ። ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ። ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቈየ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ አምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ ቊራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቊራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ዐወቀ። ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም። ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፤ “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።” ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ። እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚንቀሳቀሱ ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ። ከዚያም ኖኅ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደስ የሚያሰኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም[32] በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም። “ምድር እስካለች ድረስ፣ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት፣ አይቋረጡም።” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ፦ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል። ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ። “ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ። “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፣ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አምሳል፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሠርቶታልና። እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሠራፋ።” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንሰሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ። ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።” ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው። ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበሩ፤ ካም የከነዓን አባት ነው። ሦስቱ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከእነዚሁ ነው። ኖኅ ገበሬ ነበረና ወይን ተከለ፤[33] ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ ዕርቃኑን ተኛ። የከነዓን አባት፣ ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ። ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ፣ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን ዐወቀ፤ እንዲህም አለ፤ “ከነዓን የተረገመ ይሁን፤ ለወንድሞቹም፣ የባሪያ ባሪያ ይሁን።” ደግሞም፤ “የሴም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይባረክ፤ ከነዓንም የሴም[34] ባሪያ ይሁን።” “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የያፌትን[35] ግዛት ያስፋ፤ ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤ ከነዓንም የእርሱ[36] ባሪያ ይሁን” አለ። ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ፤ ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖሮ ሞተ። የኖኅ ልጆች የሴም፣ የካምና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ እነርሱም ራሳቸው ከጥፋት ውሃ በኋላ ወንዶች ልጆችን ወለዱ። የያፌት ልጆች፦[37] ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣ ቴራስ ናቸው። የጋሜር ልጆች፦ አስከናዝ፣ ራፋት፣ ቴርጋማ ናቸው። የያዋን ልጆች፦ ኤሊሳ፣ ተርሴስ፣ ኪቲም፣ ሮዲኢ[38] ናቸው። ከእነዚህም በየነገዳቸው፣ በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው ተከፋፍለው በባሕር ዳርና በደሴቶች፣ በየምድራቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ወጡ። የካም ልጆች፦ ኩሽ፣ ምጽራይም፣ [39]ፉጥ፣ ከነዓን ናቸው። የኩሽ ልጆች፦ ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማ፣ ሰበቅታ ናቸው። የራዕማ ልጆች፦ ሳባ፣ ድዳን ናቸው። ኩሽ የናምሩድ አባት[40] ነበረ፤ ናምሩድም በምድር ላይ ኀያል ሰው እየሆነ ሄደ። በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ብርቱ አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ናምሩድ ብርቱ አዳኝ” ይባል ነበር። የግዛቱም የመጀመሪያ ከተሞች፦ ባቢሎን፣ ኦሬክ፣ አርካድና ካልኔ ናቸው፤ እነዚህ በ[41]ሰናዖር[42] ምድር ነበሩ። ከዚያም ምድር ወደ አሦር ወጥቶ ነነዌን፣ ረሆቦትን፣[43] ካለህን እንዲሁም በነነዌና በካለህ መካከል ሬስን ቈረቈረ፤ ታላቁንም ከተማ መሠረተ። ምጽራይም፦ የሉዳማውያን፣ የዕሚማውያን፣ ላህቢያውያን፣ የነፍታሌማውያን፣ የፈትሩሲማውያን፣ ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው የኮስሉሂማውያን፣ የቀፍቶሪማውያን አባት ነበረ። ከነዓንም፦ የበኵር ልጁ[44] የሲዶን፣ የኬጢያውያን፣ የኢያቡሳውያን፣ የአሞራውያን፣ የጌርሳውያን አባት ነበረ፤ እንዲሁም የኤዊያውያን፣ የዑር ኬዋናውያን፣ የሲኒያውያን፣ የአራዴዎናውያን፣ የሰማሪናውያን፣ የአማቲያውያን አባት ነበረ። ከጊዜ በኋላ የከነዓን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤ የከነዓን ወሰን ከሲዶና አንሥቶ በጌራራ በኩል እስከ ጋዛ ይደርሳል፤ ከዚያም በሰዶም በኩል ገሞራን፣ አዳማንና ሰቦይን ይዞ እስከ ላሣ ይዘልቃል። እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የካም ዝርያዎች ናቸው። ለያፌት ታላቅ ወንድም[45] ለሴም ደግሞ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት ነው። የሴም ልጆች፦ ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ፣ አራም ናቸው። የአራም ልጆች፦ ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴር፣ ሞሶሕ ናቸው። አርፋክስድ ሳላን ወለደ፤[47] ሳላም ዔቦርን ወለደ። ለዔቦርም ሁለት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ አንደኛው ልጅ በዘመኑ ምድር ተከፍላ ስለ ነበር ፍሌቅ[48] ተባለ፤ ወንድሙም ዮቅጣን ተባለ። ዮቅጣንም፦ የኤልሞሳድ፣ የሣሌፍ፣ የሐስረሞት፣ የያራሕ፣ የሀደራም፣ የአውዛል፣ የደቅላ አባት ነበረ፤ እንዲሁም የዖባል፣ የአቢማኤል፣ የሳባ፣ የኦፊር፣ የኤውላጥ፣ የዮባል አባት ነበረ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። መኖሪያ ስፍራቸውም እስከ ሶፋር ድረስ ይዘልቃል። እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የሴም ዝርያዎች ናቸው። የኖኅ ወንዶች ልጆች ጐሣዎች እንደ ትውልዳቸው በየነገዳቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውሃ በኋላ ሕዝቦች በምድር ላይ የተሠራጩት ከእነዚሁ ነው። በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የሚናገሩትና የሚግባቡበት ቋንቋ አንድ ብቻ ነበር። ሰዎቹም ምሥራቁን[49] ይዘው ሲጓዙ፣ በሰናዖር[50] አንድ ሜዳ አግኝተው በዚያ ሰፈሩ። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “ኑ፤ ጡብ እንሥራ፤ እስኪበቃውም በእሳት እንተኵሰው” ተባባሉ። በድንጋይ ፈንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ። ከዚያም “ለስማችን መጠሪያ እንዲሆንና በምድር ላይ እንዳንበተን፣ ኑ፤ ከተማና ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንሥራ” አሉ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን ሰዎቹ ይሠሩ የነበሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ እንደ አንድ ሕዝብ አንድ ቋንቋ በመናገር ይህን ማድረግ ከጀመሩ፣ ከእንግዲህ ያቀዱትን ሁሉ ማከናወን አያዳግታቸውም። ኑ እንውረድ፤ እርስ በርሳቸውም እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።” ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድር ሁሉ ላይ በታተናቸው፤ ከተማዋንም መሥራት አቆሙ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚያ የመላውን ዓለም ቋንቋ ስለ ደበላለቀ የከተማዪቱ ስም ባቤል[51] ተባለ። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰዎቹን በምድር ሁሉ በተናቸው። የሴም ትውልድ ይህ ነው፦ ሁለት ዓመት ከጥፋት ውሃ በኋላ ሴም በ100 ዓመቱ አርፋክስድን ወለደ። ሴም፣ አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። አርፋክስድ በ35 ዓመቱ ሳላን ወለደ፤ ሳላንን ከወለደ በኋላ አርፋክስድ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶችን ወለደ። ሳላ በ30 ዓመቱ ዔቦርን ወለደ፤ ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሳላ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ዔቦር በ34 ዓመቱ ፋሌቅን ወለደ፤ ፋሌቅን ከወለደ በኋላ ዔቦር 430 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ፋሌቅ በ30 ዓመቱ ራግውን ወለደ፤ ራግውንን ከወለደ በኋላ ፋሌቅ 209 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ራግው በ32 ዓመቱ ሴሮሕን ወለደ፤ ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ራግው 207 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ሴሮሕ በ30 ዓመቱ ናኮርን ወለደ፤ ናኮርን ከወለደ በኋላ ሴሮሕ 200 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ናኮር በ29 ዓመቱ ታራን ወለደ፤ ታራን ከወለደ በኋላ ናኮር 119 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ታራ 70 ዓመት ከሆነው በኋላ አብራምን፣ ናኮርንና ሐራንን ወለደ። የታራ ትውልድ ይህ ነው፦ ታራ፣ አብራምን ናኮርንና ሐራንን ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ። ሐራን፣ አባቱ ታራ ገና በሕይወት እንዳለ በከለዳውያን ምድር በምትገኘው በተወለደባት ከተማ በዑር ሞተ። አብራምና ናኮር ሁለቱም ሚስት አገቡ፤ የአብራም ሚስት ሦራ ስትባል፣ የናኮር ሚስት ደግሞ ሚልካ ትባል ነበር፤ ሚልካም የሐራን ልጅ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነበረ። ሦራ መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም። ታራ ልጁን አብራምን፣ ሐራን የወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን እንዲሁም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነዓን ለመሄድ በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ከዑር አብረው ወጡ፤ ነገር ግን ካራን በደረሱ ጊዜ በዚያ ተቀመጡ። ታራ 205 ዓመት ኖሮ በካራን ሞተ። እግዚአብሔር (ያህዌ) አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ። የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህን እረግማለሁ፤ በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።” ስለዚህ አብራም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ሲወጣ ዕድሜው 75 ዓመት ነበረ። አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው በመጓዝ ከነዓን ምድር ገቡ። አብራም ትልቁ የሞሬ ዛፍ እስከሚገኝበት እስከ ሴኬም ድረስ በምድሪቱ ዘልቆ ሄደ። በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን በዚሁ ምድር ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት አምላክ (ያህዌ) በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠርቶ ጸለየ። አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ። በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብፅ ወረደ። ግብፅ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ ግብፃውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።” አብራም በግብፅ አገር እንደ ደረሰ ግብፃውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደሆነች አዩ፤ የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት። በእርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው። ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’ ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!” ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለ ሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት። አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብፅ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም አብሮት ነበረ። አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር። አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣ ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ። ከአብራም ጋር አብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት። ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ አብረው መኖር አልቻሉም። ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያን ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር። አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም። ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።” ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብፅ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው። ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ። አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ። ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) አብራምን እንዲህ አለው፤ ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ። ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል። እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።” አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ። አምራፌል የሰናዖር[53] ንጉሥ፣ አርዮክ የእላሳር ንጉሥ፣ ኮሎዶጎምር የኤላም ንጉሥ፣ ቲድዓል የጎይም ንጉሥ በነበሩበት ዘመን፣ ከሰዶም ንጉሥ ከበላ፣ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፣ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፣ ከሰቦይ ንጉሥ ከሰሜበር፣ እንዲሁም ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥ ጋር ለመዋጋት ወጡ። እነዚህ የኋለኞቹ አምስቱ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ፣ በጨው ባሕር[54] ተሰበሰቡ። እነርሱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ከተገዙ በኋላ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ዐመፁ። በዐሥራ አራተኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና ከርሱ ጋር የተባበሩት ነገሥታት ወጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኑሚምን በሴዊ ቂርያታይም፣ የሖር ሰዎችንም በተራራማው አገር በሴይር በረሓማ አጠገብ እስካለው እስከ ኤልፋራን ድረስ ድል አደረጓቸው። ከዚያም ተመልሰው ዓይን ሚስፖጥ ወደተባለው ወደ ቃዴስ መጡ፤ የአማሌቃውያንና በሐሴስ ታማር ይኖሩ የነበሩትን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ድል አድርገው ያዙ። ከዚያም የሰዶም፣ የገሞራ፣ የአዳማ፣ የሰቦይ እንዲሁም ዞዓር የተባለችው የቤላ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ ሰራዊታቸውን አስተባበሩ፤ እነዚህ አምስቱ፣ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፣ በጎይም ንጉሥ በቲድዓል፣ በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፣ በእላሳር ንጉሥ በኦርዩክ፣ በእነዚህ በአራቱ ላይ ዘመቱባቸው። በሲዲም ሸለቆ ብዙ የቅጥራን ጒድጓዶች ስለ ነበሩ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሲሸሹ ከሰዎቻቸው አንዳንዶቹ በነዚህ ጒድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራሮች ሸሹ። አራቱ ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ሀብትና ምግብ ሁሉ ዘርፈው ሄዱ። የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ። ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ[55] አስኮናአውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ። አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ። አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። አብራም ጠላት የማረከውን በሙሉ አስጣለ፤ የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ንብረቱን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ምርኮኞች አስመለሰ። አብራም ኮሎዶጎምርንና አብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ካህን የነበረው የሳሌም[56] ንጉሥ መልከጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ[57] ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) አብራምን ይባርክ፤ ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣ ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ይባረክ።” አብራምም ካመጣው ሁሉ ዐሥራትን ሰጠው። የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው። አብራም ግን ለሶዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ወደ ልዑል አምላክ (ኤል-ኤልዮን) እጆቼን አንሥቻለሁ፤ ‘አብራምን አበለጸግሁት’ እንዳትል፣ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አንዳች አልፈልግም። ሰዎቼ ከበሉትና ከእኔ ጋር ከሄዱት ሰዎች ድርሻ በስተቀር ለራሴ አንዳች ነገር አልቀበልም፤ አውናን፣ ኤስኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።” ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ “አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤[58] ታላቅ ዋጋህም[59] እኔው ነኝ። አብራምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ[60] የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው። “አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።” በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።” ወደ ውጪም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቊጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቊጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው። አብራም እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት። ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔ ነኝ” አለው። አብራምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ አብረህ አቅርብልኝ” አለው። አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ዋኖሷንና ርግቧን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም። አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው። ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በእርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።” ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። በዚያ ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብፅ ወንዝ[61] ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።” የአብራም ሚስት ሦራ፣ ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤ እርሷም አጋር የምትባል ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት። አብራምንም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ልጅ እንዳልወልድ አድርጎኛል። ምናልባት በእርሷ በኩል ልጆች አገኝ እንደሆን ሄደህ ከአገልጋዬ ጋር ተኛ” አለችው። አብራምም ሦራ ባለችው ተስማማ። አብራም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ሚስቱ ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ሰጠችው። አብራምም ከአጋር ጋር ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች። ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው። አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች። የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር። መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት፤ እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእርሷም ተገዥላት” አላት። ደግሞም መልአኩ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ በተጨማሪ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ችግርሽን ተመልክቶአል፤ ስሙን እስማኤል[62] ትዪዋለሽ። እርሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል፤ እጁንም ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ ያነሣል፤ ያገኘውም ሁሉ እጁን ያነሣበታል፤ ከወንድሞቹ ሁሉ ጋር እንደ ተጣላ ይኖራል።” [63] እርሷም ያናገራትን እግዚአብሔርን (ያህዌ)፣ ኤልሮኢ ብላ ጠራችው፤ ምክንያቱም “የሚያየኝን አሁን አየሁት”[64] ብላ ነበርና። ከዚህ የተነሣ የዚያ ምንጭ ስም፣ “ብኤርለሃይሮኢ”[65] ተብሎ ተጠራ፤ እስካሁንም በቃዴስና በባሬድ መካከል ይገኛል። አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም ስሙን እስማኤል ብሎ ጠራው። አብራም፣ አጋር እስማኤልን በወለደች ጊዜ ዕድሜው 86 ዓመት ነበር። አብራም ዕድሜው 99 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “እኔ ኤልሻዳይ”[66] ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ነቀፋም አይኑርብህ፤ በእኔና በአንተ መካከል የተመሠረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛለሁ።” አብራም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም[67] መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና። ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ (ኤሎሂም) እሆናለሁ። ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ።” ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ። አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል። የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ። በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል። የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን። እኔ እባርካታለሁ ከእርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።” አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። አብርሃም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “ይሁን እሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ[68] ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከእርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከእርሱ ጋር እገባለሁ። ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይስሐቅ ጋር አደርጋለሁ።” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአብርሃም ጋር መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ። በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ገረዛቸው። አብርሃም ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር። ልጁም እስማኤል ሲገረዝ 13 ዓመቱ ነበር። አብርሃምና ልጁ እስማኤል፣ ሁለቱም በዚያኑ ቀን ተገረዙ። በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ፣ በቤቱ የተወለዱትም ሆኑ ከውጭ በገንዘብ የተገዙ ከእርሱ ጋር ተገረዙ። ቀትር ላይ አብርሃም በመምሬ ትልልቅ ዛፎች አቅራቢያ በምትገኘው ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለት፤ ቀና ብሎም ሲመለከት፣ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ፤ ወዲያውም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ፣ ፈጥኖ ወደ ሰዎቹ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም እጅ ነሣ። አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ፤[69] በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ ባሪያህን አልፈህ አትሂድ፤ ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ እዚህም ከዛፉ ሥር ዐረፍ በሉ። ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ፣ እህል ቀምሳችሁ ትበረቱ ዘንድ ምግብ ላቅርብላችሁና ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ።” እነርሱም፣ “መልካም፤ እንዳልኸው አድርግ” አሉት። አብርሃም በፍጥነት ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ ገብቶ፣ “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ[70] ስልቅ ዱቄት አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት። ከዚያም ወደ መንጋው በጥድፊያ ሄዶ፣ አንድ ፍርጥም ያለ ሥጋው ገር የሆነ ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም ጥጃውን ዐርዶ አዘጋጀው። አብርሃምም እርጎ፣ ወተትና የተዘጋጀውን የጥጃ ሥጋ አቀረበላቸው፤ ሲበሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር። እነርሱም አብርሃምን፣ “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ድንኳን ውስጥ ናት” አላቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ)[71] “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተ ጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር። በዚያን ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜአቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር። ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም[72] ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች። እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች? ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት በተባለው ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።” ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች። እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት። ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቊልቊል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ወጣ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ። ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።” ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቶአል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቶአል፤ አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።” ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ቆመ ነበር።[73] አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ አምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን አትምርምን?[74] እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ[75] በቅን አይፈርድምን?” እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “በሰዶም ከተማ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ። ደግሞም አብርሃም እንዲህ አለ፤ “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ (አዶናይ) ጋር ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ፤ ለመሆኑ ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ በአምስቱ ሰዎች ምክንያት መላ ከተማዋን ታጠፋለህን?” እርሱም፣ “አርባ አምስት ጻድቃን ባገኝ አላጠፋትም” አለ። አብርሃምም እንደ ገና፣ “ምናልባት አርባ ጻድቃን ቢገኙስ?” አለ እርሱም፣ “ለአርባው ስል እምራታለሁ” አለ። ደግሞም አብርሃም፣ “ጌታዬ (አዶናይ) አይቈጣ፤ እባክህ ልናገር፤ ሠላሳ ጻድቃን ብቻ ቢገኙስ?” እርሱም፣ “ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም” ብሎ መለሰ። አብርሃምም፣ “ከጌታ (አዶናይ) ጋር እናገር ዘንድ መቼም አንዴ ደፍሬአለሁና ምናልባት ሃያ ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እርሱም፣ “ሃያ ቢገኙ፣ ለእነርሱ ስል እምራታለሁ” አለ። አብርሃምም፣ “ጌታዬ (አዶናይ) አይቈጣ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ ምናልባት ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እርሱም “ስለ ዐሥሩ ስል አላጠፋትም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአብርሃም ጋር ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግምባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው። እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ አድራችሁም ጧት በማለዳ ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው። እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት። ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ። ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከያካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት። ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት። ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቶ፣ እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ። እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።” እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳናደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ። ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ። ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ። ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤ ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።” ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች[76] የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው። ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት። ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው። እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለበለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው። ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤[77] እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤ እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል። እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም። አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር[78] ተባለ። ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው። እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው። የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። አብርሃም በማግስቱ፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሞ ወደነበረበት ቦታ ሄደ። ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቊልቊል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ። እንደዚህ አድርጐ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን አሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው። ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ አደረገ። አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቶአል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ አብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም። ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።” በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር። በማግስቱም ታላቂቱ ልጅ ታናሺቱን፣ “እኔ ትናንትና ማታ ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ፤ ዛሬም እንደ ገና የወይን ጠጅ እናጠጣው፤ አንቺም ደግሞ ከእርሱ ዘንድ ገብተሽ ተኚ፤ በዚህም የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ከአባታችን ዘር ማትረፍ እንችላለን” አለቻት። በዚያችም ምሽት ደግሞ አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ትንሿ ልጁም ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር። ስለዚህ ሁለቱም የሎጥ ሴት ልጆች ከአባታቸው አረገዙ። ትልቋ ልጁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ ሞዓባውያን[79] አባት ነው። ትንሿ ልጁም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ[80] ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ አሞናውያን አባት ነው። አብርሃም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ አካባቢ ሄዶ በቃዴስና በሱር መካከል ሰፈረ፤ ለጥቂት ጊዜም በጌራራ ተቀመጠ። በዚያም አብርሃም ሚስቱን ሣራን፣ “እህቴ ናት” ይል ነበር። ስለዚህ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ መልእክተኛ ልኮ ሣራን ወሰዳት። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በአንድ ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ፣ “እነሆ፤ በወሰድሃት ሴት ምክንያት ምውት ነህ፤ እርሷ ባለ ባል ናት” አለው። አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን? ‘እኅቴ ናት’ ያለኝ ራሱ አይደለምን? ደግሞስ ራሷም ብትሆን፣ ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረግሁት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በሕልሙ እንዲህ አለው፤ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው። አሁንም ሚስቱን ለሰውዬው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ።” በማግስቱም ማለዳ፣ አቢሜሌክ ሹማምቱን ሁሉ ጠርቶ፣ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነርሱም ታላቅ ፍርሀት አደረባቸው። ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣብህን? በእውነቱ መደረግ የማይገባውን ነው ያደረግህብን።” ከዚያም አቢሜሌክ፣ “ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው። አብርሃምም አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “እዚህ ቦታ ፈሪሀ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አለመኖሩን ተገነዘብሁ፤ ሰዎቹም ለሚስቴ ሲሉ ይገድሉኛል ብዬ ሠጋሁ፤ ደግሞም እኮ በእርግጥ እኅቴ ናት፤ ከአንድ እናት ባንወለድም በአባት አንድ ነን፤ ኋላም አገባኋት። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አዞኝ ከአባቴ ቤት ወጥቼ በየአገሩ ስዞር፣ ‘ለእኔ ያለሽን ፍቅር በዚህ ግለጭልኝ፤ በየደረስንበት ስፍራ ሁሉ “እርሱ ወንድሜ ነው” በዪ’ ብያት ነበር።” ከዚያም አቢሜሌክ፣ በጎችና የቀንድ ከብቶች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። አቢሜሌክም አብርሃምን፣ “እነሆ፤ አገሬ አገርህ ናት፤ በፈቀድህበት ስፍራ መኖር ትችላለህ” አለው። ሣራንም፣ “እነሆ፤ ለወንድምሽ ለአብርሃም 1000 ጥሬ ብር[81] እሰጠዋለሁ፤ ይህም በአንቺ ላይ ለተፈጸመው በደል ካሣ እንዲሆንና አብረውሽ ያሉ ሁሉ እንዲያውቁት ነው፤ በዚህም ንጽሕናሽ ይረጋገጣል” አላት። ከዚያም አብርሃም ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት አገልጋዮቹን ፈወሳቸው፤ እንደ ገናም ልጅ ለመውለድ በቁ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት፣ በአቢሜሌክ ቤት የሚገኙትን ሴቶች ማሕፀናቸውን ሁሉ ዘግቶ ነበርና። እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት። ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይስሐቅ[82] አለው። አብርሃም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባዘዘው መሠረት ልጁን ይስሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው። አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ። ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች። ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች። ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፣ በይስሐቅ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች።” እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” በማግስቱ አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሞአት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም[83] እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጒድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከልጁ ጋር ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብፅ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው። በዚያን ጊዜ አቢሜሊክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ነው። እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚች ምድር ቸርነት አድርግ።” አብርሃምም፣ “እሺ፤ እምላለሁ” አለ። ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮቹ ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጒድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት። አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው። ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ። አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤ አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድ ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው። አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጒድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች እንካ ተቀበለኝ” አለው። ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ[84] ተባለ። በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ። አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለም አምላክን (ኤል ኦላም) ስም ጠራ። አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረጅም ጊዜ በእንግድነት ኖረ። ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጒዞውን ጀመረ፤ በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው። አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው። አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው። ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ። አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል (ኤሎሂም ይሬህሎ)” አለው። ሁለቱም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም፤ አብርሃም፤” ብሎ ጠራው፤ አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጒዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው። አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት በቊጥቋጦ መካከል ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም (ያህዌ) በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና፣ በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።” ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ። ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች። እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት ቀሙኤል፣ ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።” ባቱኤልም ርብቃን ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው። ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ኖረች፤ በከነዓን ምድር፣ በቂርያት አርባቅ ማለትም በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያለቅስና ሊያዝን መጣ። ከዚያም አብርሃም ከተቀመጠበት ከሚስቱ ሬሳ አጠገብ ተነሣ፤ ኬጢያውያንንም[85] እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሆኜ በመካከላችሁ የምኖር ነኝና ለመቃብር የምትሆን ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም ሬሳ ልቅበርበት።” ኬጢያውያንም ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ስማን ጌታዬ፤ አንተ እኮ በእኛ ዘንድ እንደ ኀያል መስፍን ነህ፤ ከመቃብር ቦታችን በመረጥኸው ስፍራ ሬሳህን መቅበር ትችላለህ፤ ማናችንም ብንሆን የሞተብህን ሰው እንዳትቀብርበት የመቃብር ቦታችንን አንከለክልህም።” ከዚያም አብርሃም ተነሥቶ የአገሬውን ሕዝብ፣ ኬጢያውያንን እጅ ነሣ፤ እንዲህም አላቸው፤ እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ፣ አንዴ ስሙኝና የሰዓርን ልጅ ኤፍሮንን ስለ እኔ ሆናችሁ ለምኑልኝ። ይኸውም በዕርሻው ድንበር ላይ ያለችውን መክፈላ የተባለችውን ዋሻውን እንዲሸጥልኝ ነው፤ በመካከላችሁም የመቃብር ቦታ እንድትሆነኝ በሙሉ ዋጋ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ። ኬጢያዊው ኤፍሮንም እዚያው መካከላቸው ተቀምጦ ስለ ነበር፣ ወደ ከተማው በር መግቢያ መጥተው የተሰበሰቡት ኬጢውያን በሙሉ እየሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እንዲህ አይደለም ጌታዬ፤ አድምጠኝ፤ ዕርሻውን በውስጡ ካለው ዋሻ ጋር ውሰደው፤ እነሆ፤ በወገኖቼ ኬጢያውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ፤[86] ሬሳህን ቅበርበት።” አብርሃም እንደ ገና የአገሬውን ሕዝብ እጅ ነሣና ሁሉም እየሰሙት፣ የዕርሻውን ቦታ ዋጋ ልክፈል፤ እባክህን ተቀበለኝና ሬሳዬን ልቅበርበት” አለው። ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የመሬቱ ዋጋማ አራት መቶ ጥሬ ብር[87] ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በአንተ መካከል ምን ቁም ነገር አለው? ይልቅስ ሬሳህን ቅበርበት” አለው። አብርሃምም፣ ኤፍሮን በኬጢያውያን ፊት በተናገረው ዋጋ ተስማማ፤ በወቅቱም የንግድ መለኪያ መሠረት አራት መቶ ጥሬ ብር መዘነለት። በዚህ ሁኔታ፣ በመምሬ አጠገብ በመክፈላ ያለው የኤፍሮን ዕርሻ ቦታ ከነዋሻው በክልሉ ካሉት ዛፎች ሁሉ ጭምር ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈ፤ ወደ ከተማው በር በመጡት ኬጢያውያንም ሁሉ ፊት የአብርሃም ንብረት መሆኑም ተረጋገጠለት። ከዚህም በኋላ አብርሃም በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ መክፈላ በተባለች ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ የሚስቱን የሣራን ሬሳ ቀበረ፤ ይህችም ኬብሮን ናት። ስለዚህ ዕርሻውና ውስጡ የሚገኘው ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን፣ ከኬጢያውያን ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈለት። በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው። አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ[88] የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤ ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ማልልኝ። ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።” አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው። አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤ ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ። ሴቲቱ አብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው። ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጐ ስለዚህ ጒዳይ ማለለት። አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዙ። እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ጥላ የበረደበት፣ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነበር። ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጒዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው፤ እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች። ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች። ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጒድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው። አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዱን አሳክቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጂቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር። ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል[89] የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል[90] የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣ “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት። እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤ ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው። ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተመሰገነ ይሁን።” ልጂቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች። ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጒድጓድ ፈጥኖ ሄደ። እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው። ሰውየው ከላባ ጋር ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለእርሱና አብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው። ለሰውየውም ማዕድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጒዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ። ላባም፣ “እሺ፤ ተናገር” አለው። እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ[91] ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል። ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፤ ‘ከዚህ ከምኖርበት አገር፣ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር ልጄን አታጋባው፤ ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት’። “እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት። “እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል። ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጂቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ። “እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጒድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጒዳይ አቃናልኝ፤ እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣ እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’ “በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት። “እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሸዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች። “ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ” ብዬ ጠየቅኋት። “እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ። “ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት። ተደፍቼም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝ የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አመሰገንሁ። እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።” ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።” የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ። ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። እርሱና አብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤ በማግስቱ ጠዋት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ። ወንድሟና እናቷም፣ “ልጂቷ ከእኛ ጋር ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ[92] ትችላለች።” ብለው መለሱ። እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፣ “ለማናቸውም ልጂቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ። ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት። እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች። ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋር፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤ “እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”። ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ። በዚህን ጊዜ፣ ይስሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር። እርሱም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና[93] ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ። ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይስሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤ አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች። አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባትም፤ ሚስት ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ።[94] እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት። ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው። የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳድ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይስሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው። አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን[95] የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ። አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይስሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር። ግብፃዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው። የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦ የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣ ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣ ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣ ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ። እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው። እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።[96] የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች። ይስሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለመጠየቅ ሄደች። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤ “ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀንዋ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጒር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው[97] ተባለ። ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ[98] ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይስሐቅ የሥልሳ ዓመት ሰው ነበር። ልጆቹም አደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። ይስሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር። አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም፣ “እነሆ፣ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ። ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት። ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት። ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከደረሰው ራብ ሌላ፣ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። ይስሐቅም የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ ወደሚኖርበት ወደ ጌራራ ሄደ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለይስሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብፅ አትውረድ፤ ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ። ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ፤ ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።” ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በእርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር። ይስሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይስሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት እኅቴ ናት ትላለህ?” አለው። ይስሐቅም፣ “በእርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው። አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሩአቸውን የውሃ ጒድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑዋቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው። ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው። የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጒድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ። የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይስሐቅ ያን የውሃ ጒድጓድ ኤሴቅ[99] ብሎ ጠራው፤ በጒድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጒድጓዱን ስጥና[100] ብሎ ጠራው። ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጒድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጒድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት[101] ብሎ ጠራው። ከዚያም ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። ይስሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ። አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ከጌራራ ተነሥቶ ይስሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ። ይስሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካካል የሚጸና ውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋር ስምምነት እናድርግ፤ አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባርኮሃል።” ይስሐቅም ድግስ ደግሶ፣ አበላቸው፤ አጠጣቸው። በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ። በዚያኑ ዕለት፣ የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጒድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት። እርሱም የውሃውን ጒድጓድ ሳቤህ[102] አለው፤ ከዚያም የተነሣ የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ ይጠራል። ዔሳው አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ የኬጢያዊውን የብኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የኬጢያዊውን የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትን አገባ፤ በእነዚህም ሴቶች ምክንያት የይስሐቅና የርብቃ ልብ ያዝን ነበር። ይስሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው። እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። ይስሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን ዐላውቅም ስለዚህ የአደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰሮጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ። ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።” ይስሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣ ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣ ‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤ ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ። ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ፣ የሚወደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤ እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ፣ ይዘህለት ግባና ይብላ።” ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጒራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው። ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።” እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው። እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት። ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው። እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው። ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ፤ አለ፤ ይስሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው። ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስቲ ቀና በልና እንድትመርቀኝ አድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ። ይስሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀናህና መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት። ይስሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በእርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስቲ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ። እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጒራም ስለሆኑ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው። ይስሐቅም፣ “በእርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ። ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ አድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው። ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም። ከዚያም አባቱ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው። ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤ “እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ባረከው፣ እንደ መስክ መዐዛ ነው። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰማይን ጠል፣ የምድርንም በረከት፣ የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ። መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤ የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤ የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።” ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ። እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው። አባቱ ይስሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በእርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው። ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው። ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው። ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ። ይስሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት። ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። አባቱ ይስሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “መኖሪያህ ከምድር በረከት፣ ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤ በሰይፍ ትኖራለህ፤ የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ። አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣ ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣ ወዲያ ትጥላለህ።” አባቱ ያቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቦአል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ አሰበ። ርብቃ፣ ታላቁ ልጇ ዔሳው ያሰበው በተነገራት ጊዜ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ጊዜ እየጠበቀ ነው፤ አሁንም፣ ልጄ ሆይ፤ እኔ የምልህን አድርግ፤ በካራን ምድር ወደሚኖረው ወደ ላባ ቶሎ ሽሽ። የወንድምህ ቍጣ እስከሚበርድ እዚያው ቈይ፤ ነገር ግን ቍጣው በርዶለት ያደረግህበትን ከረሳ በኋላ፣ እንድትመለስ እልክብህና ትመጣለህ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?” ከዚያም ርብቃ ይስሐቅን፣ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው። ይስሐቅ ያዕቆብን አስጠርቶ ከመረቀው[103] በኋላ፣ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ። አሁኑኑ ተነሥተህ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጎትህ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዲቷን አግባ። ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ[104] ይባርክህ፤ ብዙ ሕዝብ እስክትሆን ድረስ ልጆች አፍራ፤ ዘርህን ያብዛው። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ። ይስሐቅም ያዕቆብን በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ወደ ሆነው ወደ ሶርያዊው የባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ላከው። ዔሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ ሚስት እንዲያገባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ እንደ ላከውና በባረከውም ጊዜ ከነዓናዊት ሴት እንዳያገባ ትእዛዝ እንደ ሰጠው ሰማ። ያዕቆብ የአባቱንና የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ። በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤ ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ። ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ። በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከጫፉ ላይ[105] ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ። ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። እርሱም በፍርሀት፣ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህስ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቤት መሆን አለበት፤ የሰማይ ደጅ ነው” አለ። ያዕቆብም በማግስቱ ማልዶ ተነሣ፣ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ አንሥቶ እንደ ሐውልት አቆመው፤ በዐናቱም ላይ የወይራ ዘይት አፈሰሰበት። ያንን ቦታ ቤቴል[106] ብሎ ሰየመው፤ ቀደም ሲል ግን የከተማዪቱ ስም ሎዛ ነበር። ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበትም መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላው ምግብ፣ የምለብሰውን ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ ቤት በደኅና ቢመልሰኝ፣ እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ይሆናል፤ ይህ ሐውልት አድርጌ ያቆምሁት ድንጋይ፣ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሀብት ሁሉ፣ ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ።” ያዕቆብም ጒዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ። እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጒድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጒድጓድ ሲሆን፣ የጒድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው። መንጎቹ ሁሉ በጒድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጒድጓዱን አፍ ይገጥሙታል። ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት። እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት። ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት። ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው። እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጒድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በስተቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ። ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጒድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጒድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ። ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው። ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ፣ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቊራጭ ነህ” አለው። ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ አብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣ ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው። ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። ልያ ዐይነ ልም[107] ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር። ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው። ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው። ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቶአል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው። ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ። ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት። ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጒድ ሠራኸኝ? ያገለገልኹህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ ይህን የጫጒላ ሳምንት ፈጽምና፣ ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን። ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፤ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤ ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጡር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት። ያዕቆብ ከራሔልም ጋር ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል[108] አለችው። እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን[109] ብላ ጠራችው። አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ[110] ብላ ጠራችው። እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ[111] ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች። ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ስለዚህ ያዕቆብን፣ “ልጅ ስጠኝ፤ አለበለዚያ እሞታለሁ” አለችው። ያዕቆብም ራሔልን ተቈጥቶ “እኔ እንዳትወልጂ ያደረገሽን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መሰልኹሽን?” አላት። እርሷም፣ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው። ስለዚህም አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት። ራሔልም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ አወጣችለት። የራሔል አገልጋይ ባላ እንደ ገና ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። ራሔልም፣ “እኅቴን ብርቱ ትግል ገጥሜ አሸነፍሁ” አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ አወጣችለት። ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደ ተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው። የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምን ዐይነት መታደል[112] ነው” አለች፤ ስሙንም ጋድ[113] ብላ አወጣችለት። የልያም አገልጋይ ዘለፋ፤ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምንኛ ደስተኛ ሆንሁ ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛዋ ይሉኛል” አለች፤ ስሙንም አሴር[114] ብላ አወጣችለት። ስንዴ በሚታጨድበት ወቅት፣ ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ እንኮይም አግኝቶ ለእናቱ ለልያ አመጣላት። ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። ልያም፣ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት። በዚያች ምሽት ያዕቆብ ከዕርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው አዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው፤ ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከእርሷ ጋር አደረ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም አምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። ልያም፣ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ክሶኛል” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር[115] ብላ አወጣችለት። ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። እርሷም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በከበረ ስጦታ ዐድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል”። አለች፤ ስሙንም ዛብሎን[116] አለችው። ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስምዋንም ዲና አለቻት። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ራሔልን ዐሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ ማሕፀንዋን ከፈተላት። ከዚያም ፀንሳ፣ ወንድ ልጅ ወለደችና “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤ ስሙንም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ ስትል፣ ዮሴፍ”[117] አለችው። ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፤ “ወደ ገዛ ቤቴ፣ ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ፤ የድካሜ ዋጋ የሆኑትን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ይዤአቸው ልሂድ፤ መቼም የቱን ያህል እንዳገለገልኹህ ታውቃለህ” አለው። ላባም እንዲህ አለው፤ “በጎ ፈቃድህ ቢሆን፣ እባክህ እዚሁ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ በንግርት ተረድቻለሁ፤[118] ይልቅስ ይገባኛል የምትለውን ደሞዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ።” ያዕቆብም እንዲህ አለው፤ “መቼም እንዴት እንዳገለገልሁህ፣ ከብቶችህ በእኔ ጥበቃ ምን ያህል እንደ ተመቻቸው አንተ ታውቃለህ። እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበረው ሀብትህ ዛሬ ተትረፍርፎአል፣ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ስለ ራሴ ቤት የማስበው መቼ ነው?” ላባም፣ “ታዲያ ምን ልስጥህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ምንም አትስጠኝ፤ ነገር ግን የምጠይቅህን አንዲት ነገር ብቻ ብታደርግልኝ ከብቶችህን ማገዴን እቀጥላለሁ፤ በመንጎቹ መካከል ዛሬ ልዘዋወርና ከበጎቹ መካከል ዝንጒርጒር የሆኑትን፣ ነቍጣ ያለባቸውንና ጥቋቁሮቹን እንዲሁም ከፍየሎቹ ነቍጣ ያለባቸውንና ዝንጒርጒሮቹን ልምረጥ፤ እነዚህ ደሞዜ ይሁኑ። ወደ ፊት ደሞዜን ለመቈጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ በመንጎቼ መካከል ዝንጒርጒር ወይም ነቍጣ የሌለበት ፍየል፣ ወይም ጥቁር ያልሆነ ቢገኝ ያ እንደ ተሰረቀ ይቈጠር”። ላባም፣ “እሺ፣ ይሁን፤ ባልኸው ተስማምቼአለሁ” አለው። ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ከተባት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቍጣ ያለባቸውን ሁሉ፣ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቍጣ ያለባቸውን ዝንጒርጒር የሆኑትን ሁሉ፣ ማንኛውንም ነጭ ያለበትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቁር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው። ከዚያም በእርሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ማገዱን ቀጠለ። ነገር ግን ያዕቆብ እርጥብ የልብን፣ የለውዝንና የኤርሞን በትሮች ወሰደ፤ ቅርፊታቸውንም በቀጭን ልጦ እያነሣ የበትሮቹ ግንድ ነጩ እንዲታይ፣ ሽመልመሌ መልክ እንዲኖራቸው አደረገ። የላጣቸውንም በትሮች መንጎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው በማጠጫ ገንዳዎቹ ሁሉ አስቀመጠ። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣ በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ። ያዕቆብ ግልገሎቹን ለብቻ ለያቸው፤ የቀሩትንም የላባ መንጎች ሽመልመሌና ጥቋቁር በሆኑት ትይዩ አቆማቸው፤ በዚህም መሠረት የራሱ መንጋ ከላባ መንጋ ጋር እንዳይቀላቀል ለብቻ ለየ። ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠበጡበት ጊዜ፣ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎቹ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤ ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን፣ በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ። በዚህም ሁኔታ ይህ ሰው እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት ሆነ። የላባ ወንዶች ልጆች፣ “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት እንዳለ ወስዶታል፤ ይህ ሁሉ እርሱ ያካበተውም ሀብት ከአባታችን የተገኘ ነው” እያሉ ሲያወሩ ያዕቆብ ሰማ። የላባ አመለካከት ከቀድሞው የተለወጠበት መሆኑንም ያዕቆብ ተረዳ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህና ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) አልተለየኝም፤ መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም። አባታችሁ ደሞዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጎዳኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አልፈቀደለትም። እርሱ፣ ‘ደሞዝህ ዝንጒርጒሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደሞዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ። “እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ። የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት። እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤ የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ (ኤል) እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።” ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “ከአባታችን ሀብት የምናገኘው ምን ውርስ አለ? እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሸጦናል፣ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የነገረህን ሁሉ አድርግ።” ከዚያም ያዕቆብ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደ ፊት አስቀደመ፤ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጒዞውን ቀጠለ። ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ሳለ፣ ራሔል የአባቷን ቤት የጣዖታት ምስል ሰረቀች። ያዕቆብም ቢሆን፣ መኰብለሉን ለሶርያዊው ለላባ ሳይገልጥለት በመቅረቱ አታልሎታል። ያዕቆብ የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይዞ፣ የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኰረብታማው አገር፣ ወደ ገለዓድ አመራ። የያዕቆብ መኰብለል ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው። ላባ ዘመዶቹን ይዞ ተነሣ፤ ያዕቆብንም ሰባት ቀን ተከታትሎ ገለዓድ በተባለ ኰረብታማ አገር ደረሰበት። ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሶርያዊው ለላባ በሕልም ተገልጦ፣ “ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ፣ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኰረብታማ አገር ድንኳኑን ተክሎ ሳለ፣ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም በዚያው ሰፈሩ። ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ምን ማድረግህ ነው? አታልለኸኛል፤ ልጆቼን የጦር ምርኮኛ ይመስል አካልበህ ወሰድሃቸው። ለመሆኑ ለምን ተደብቀህ ሄድህ? ለምንስ አታለልኸኝ? ብትነግረኝ ኖሮ፣ በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና አልሸኝህም ነበር? የልጆቼን ልጆችና ልጆቼንም ስሜ ብሰናበት ምን ነበረበት? የሠራኸው የጅል ሥራ ነው። ልጐዳችሁ እችል ነበር፤ ዳሩ ግን ባለፈው ሌሊት የአባታችሁ አምላክ (ኤሎሂም) ‘ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ አለኝ። አንተ ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለ ናፈቅህ ሄደሃል፤ ነገር ግን የቤቴን የጣዖት ምስል የሰረቅኸው ለምንድ ነው?” ያዕቆብም ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶች ልጆችህን በኀይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው። ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖታት ምስል ደብቆ የተገኘ ሰው ካለ ይሙት። ያንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” ይህን ሲል፣ ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር። ላባም ወደ ያዕቆብ፣ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ደንገጡሮቿ ድንኳኖች ገባ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም። ከልያ ድንኳን ከወጣ በኋላ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። ራሔል የጣዖታቱን ምስል ከግመሏ ኮርቻ ሥር ሸሽጋ፣ በላዩ ተቀምጣበት ነበር፤ ላባም ድንኳኑን አንድ በአንድ በርብሮ ምንም ሊያገኝ አልቻለም። ራሔልም አባቷን፣ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቈጣ፤ የወር አበባዬ መጥቶ ነው።” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖታቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቈጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሰው፤ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኀጢአቴ ምን ቢሆን ነው? ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ፣ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን። ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከመንጋህ አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም። አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር እንጂ፣ ትራፊውን ለምልክትነት አምጥቼ አላውቅም፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል። ቀን በሐሩር ሌሊት በቊር ተቃጠልሁ፤ እንቅልፍም በዐይኔ አልዞር አለ፤ ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለ መንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠኽብኛል። የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም)፣ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅም ፍርሀት ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን መከራዬን አይቶ፣ ልፋቴን ተመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።” ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶቹም፣ ልጆቹም የእኔው ልጆች ናቸው፣ መንጎቹም ቢሆኑ የራሴ ናቸው። ታዲያ፣ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ? በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።” ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤ ከዚያም ዘመዶቹን፣ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ። ላባም ክምር ድንጋዩን ይጋርሠሀዱታ[119] ብሎ ጠራው፤ ያዕቆብ ደግሞ ገለዓድ[120] አለው። ላባም “ይህ ክምር ድንጋይ በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለው። ጋልዒድ ተብሎ የተጠራውም በዚሁ ምክንያት ነው፤ ደግሞም ምጽጳ[121] ተባለ፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎአልና፤ “ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም ሌሎች ሚስቶች በላያቸው ላይ ብታገባ፣ ማንም ከእኛ ጋር ባይኖርም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአንተና በእኔ መካከል ምስክር መሆኑን አትርሳ።” ደግሞም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ክምር ድንጋዩ እነሆ፤ በአንተና በእኔ መካከል ያቆምሁትም ሐውልት እነሆ፤ ይህን ክምር ድንጋይ አልፌ አንተን ለማጥቃት ላልመጣ፣ አንተም ይህን ክምር ድንጋይና ይህን ሐውልት አልፈህ እኔን ለማጥቃት ላትመጣ፣ ይህ ክምር ድንጋይ ምስክር ነው፤ ይህም ሐውልት ምስክር ነው። የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ (ኤሎሂም) በመካከላችን ይፍረድብን”። ስለዚህ ያዕቆብ በአባቱ በይስሐቅ ፍርሀት ማለ። ያዕቆብ በኰረብታማው አገር ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው፤ እነርሱም ከበሉ በኋላ እዚያው አደሩ። በማግስቱም ማለዳ ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም፣ ወደ አገሩ ተመለሰ። ያዕቆብም ደግሞ ጒዞውን ቀጠለ፤ የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መላእክት ተገናኙት፤ ባያቸውም ጊዜ፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦታ ስም መሃናይም[122] አለው። ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሎአል በሉት፤ “ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስከ አሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤ ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድና የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በጎ ፈቃድህን እንዳገኝ በማሰብ ነው።” የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ሊቀበልህ በመምጣት ላይ ነው፤ አራት መቶ ሰዎችም አብረውት አሉ” አሉት። ያዕቆብም በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተውጦ፣ አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁለት ቦታ[123] ከፈላቸው፤ በጎቹን ፍየሎቹን ከብቶቹንና ግመሎቹንም ሁለት ቦታ ከፈላቸው፣ “ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል[124] ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ አስቦ ነበር። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ። ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤ ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።” በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው አደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻ እነዚህን መረጠ፦ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች። እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዱአቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎቹንም፣ “እናንተ ቀድማችሁኝ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዱአቸው” አላቸው። ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ዔሳው አግኝቶህ፣ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተ ኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው፣” እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎችን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤ በተለይም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለትን አትዘንጉ።” ይህንም ያዘዘው፣ “ዔሳው ከእኔ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል” ብሎ ስላሰበ ነበር። ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከእርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩበት ቦታ አደረ። በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ። ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ። ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። በዚያን ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለ ሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ። ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል[125] እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው። ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። ሰውዬውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው። ስለዚህ ያዕቆብ፣ “እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል[126] አለው። ጵኒኤልንም[127] እንዳለፈ ፀሓይ ወጣችበት፤ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሹልዳን ከጭኑ ጋር የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም በጭኑ መጋጠሚያ ላይ ያለው የያዕቆብ ሹልዳ ተነክቶ ነበር። ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ልጆቹን ለልያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮች አከፋፈላቸው። ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ። እርሱ ራሱም ቀድሞአቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤ ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ። ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው። ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው አለው። ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት የማየት ያህል እቈጥረዋለሁ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብኹልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ። ዔሳውም “በል ተነሥና ጒዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው። ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ። ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጒዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።” ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው። ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ። ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት[128] ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ። ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ በከነዓን ወዳለችው ወደ ሴኬም በደኅና ደረሰ፤[129] በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ ከኤሞር ልጆች በመቶ ጥሬ ብር ገዛ፤ ኤሞርም የሴኬም አባት ነበር። በዚያም መሠዊያ አቁሞ፣ ኤል ኤሎሄ እስራኤል[130] ብሎ ጠራው። ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፣ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች። ሴኬም የተባለው የአገሩ ገዢ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ባያት ጊዜ ይዞ በማስገደድ ደፈራት። ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጂቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት። ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። ያዕቆብ፣ ልጁን ዲናን ሴኬም እንዳስነወራት ሰማ፤ በዚህ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ ከብቶቹን በመስክ ያግዱ ነበር፤ ያዕቆብም ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ታግሦ ቈየ። ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ። የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም፣ የያቆብን ልጅ ስለደፈረ ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ። ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልቡ በልጃችሁ ፍቅር ተነድፎአል፤ እባካችሁ እንዲያገባት ፍቀዱለት። በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችሁን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ። አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱባት፤[131] ሀብት ንብረትም አፍሩባት።” ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤ ጥሎሽ ብትሉኝ ጥሎሽ፣ ስጦታ ብትሉም የፈለጋችሁትን ያህል እሰጣለሁ፣ ብቻ ልጂቱን እንዳገባ ፍቀዱልኝ።” የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም፣ በእኅታቸው በዲና ላይ ስለ ተፈጸመው ነውር፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር መልስ ሰጡ፤ እንዲህም አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይህም ወንዶቻችሁን ሁሉ ገርዛችሁ እኛን የመሰላችሁ እንደሆነ ነው። ከዚያ በኋላ ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ አብረን እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። በመገረዙ የማትስማሙ ከሆነ ግን ልጃችንን[132] ይዘን እንሄዳለን።” ያቀረቡትም ሐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው። ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለ ነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤ እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን ናቸው፤ በአገራችን እንዲኖሩ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ያገባሉ። ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው አብረውን ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደሆነ ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸው ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፤ እነርሱም አብረውን ይኑሩ።” ከከተማዪቱ በር ውጪ የተሰበሰቡት ሁሉ በኤሞርና በልጁ በሴኬም ሐሳብ ተስማሙ፤ በከተማዪቱም ያሉት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቍስል ገና ትኵስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዘው ሳይታሰብ ወደ ከተማዪቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው። ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ። የያዕቆብ ልጆች ሁሉ በሬሳ ላይ እየተረማመዱ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ[133] ዘረፉ። የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዪቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤ ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃኖቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ። ያዕቆብም ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በዚህ አገር በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ዘንድ እንደ ጥምብ አስቈጠራችሁኝ፣ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። እኛ በቍጥር አነስተኞች ነን፤ ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” እነርሱ ግን፣ “ታዲያ፤ እኅታችንን እንደ ዝሙት አዳሪ ይድፈራት?” አሉት። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያዕቆብን፣ “ተነሥና ወደ ቤቴል ውጣ፤ እዚያም ተቀመጥ፤ ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ (ኤል) በዚያ መሠዊያ ሥራ” አለው። ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና አብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ። ተነሥተን ወደ ቤቴል እንውጣ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፣ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ (ኤል) መሠዊያ እሠራለሁ።” ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጒትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ወርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። ያንንም ቦታ ለቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሀትና ድንጋጤ ስለ ለቀቀባቸው ያሳደዳቸው አልነበረም። ያዕቆብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ፣ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ። ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል-ቤቴል[134] አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር። በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፤ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው የዋርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሎንባኩት[135] ተባለ። ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ[136] ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል[137] ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው። ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ማድረግ የሚችል[138] አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብ እግዚእብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፤ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት። ያዕቆብም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል[139] ብሎ ጠራው። ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት። ምጡ አስጨንቆአት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት። እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ[140] አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም[141] አለው። ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተልሔም ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው። እስራኤልም ጒዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ። እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ። ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦ የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤ የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤ የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር ናቸው። እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያት አርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት። ይስሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት። ኤዶም የተባለው የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፦ ዔሳው ከከነዓን ሴቶች አገባ፤ እነርሱም፦ የኬጢያዊው የዔሎን ልጅ ዓዳን፣ የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳት አህሊባማ፣ እንዲሁም የነባዮት እኅት የሆነችው የእስማኤል ልጅ ቤሴሞት ነበሩ። ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደችለት፤ ቤሴሞት ደግሞ ራጉኤልን ወለደችለት። እንደዚሁም አህሊባማ የዑስን፣ የዕላምንና ቆሬን ወለደችለት፤ እነዚህ ዔሳው በከነዓን አገር የወለዳቸው ልጆች ናቸው። ዔሳው ሚስቶቹን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ ቤተ ሰቦቹን በሙሉ እንደዚሁም የቀንድ ከብቶቹንና ሌሎቹንም እንሰሳት ሁሉ በከነዓን ምድር ያፈራው ሀብት እንዳለ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። ብዙ ሀብት ስለ ነበራቸው አብረው መኖር አልቻሉም፤ የነበሩበትም ስፍራ ከከብቶቻቸው ብዛት የተነሣ ሊበቃቸው አልቻለም። ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው መኖሪያውን በተራራማው አገር በሴይር አደረገ። በሴይር ተራራማ አገር የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት፣ የዔሳው ዝርያዎች እነዚህ ናቸው፤ የዔሳው ልጆች ስም፦ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝና የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጅ ራጉኤል፤ የኤልፋዝ ልጆች፦ ቴማን፣ ኦማር፣ ስፎ፣ ጎቶምና ቄኔዝ፤ የዔሳው ልጅ ኤልፋዝ ትምናዕ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ እርሷም አማሌቅን ወለደችለት፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ የልጅ ልጆች እነዚህ ናቸው። የራጉኤል ልጆች፦ ናሖት፣ ዛራ፣ ሣማና ሚዛህ፤ እነዚህ ደግሞ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት የልጅ ልጆች ናቸው። የፅብዖን የልጅ ልጅ፣ የዓና ልጅ የዔሳው ሚስት አህሊባማ ለዔሳው የወለደቻቸው ልጆች፦ የዑስ፣ የዕላማና ቆሬ፤ ከዔሳው ዝርያዎች እነዚህ የነገድ አለቆች ነበሩ፤ የዔሳው የበኵር ልጅ የኤልፋዝ ልጆች፦ አለቃ ቴማን፣ አለቃ ኦማር፣ አለቃ ስፎ፣ አለቃ ቄኔዝ፣ አለቃ ቆሬ፣[142] አለቃ ጎቶምና አለቃ አማሌቅ፤ እነዚህ በኤዶም ምድር ከኤልፋዝ የተገኙ የነገድ አለቆች፣ የዓዳ የልጅ ልጆች ነበሩ። የዔሳው ልጅ ራጉኤል ልጆች፦ አለቃ ናሖት፣ አለቃ ዛራ፣ አለቃ ሣማና አለቃ ሚዛህ፤ እነዚህ በኤዶም ምድር ከራጉኤል የተገኙ የነገድ አለቆች፣ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት የልጅ ልጅ ነበሩ። የዔሳው ሚስት የአህሊባም ልጆች፦ አለቃ የዑስ፣ አለቃ የዕላማና፣ አለቃ ቆሬ፤ እነዚህ ከዓና ልጅ፣ ከዔሳው ሚስት ከአህሊባማ የተገኙ የነገድ አለቆች ነበሩ። እነዚህም ኤዶም የተባለው የዔሳው ልጆችና የነገድ አለቆቻቸው ነበሩ። በዚያች ምድር ይኖሩ የነበሩ የሖሪው የሴይር ልጆች እነዚህ ነበሩ፦ ሎጣን፣ ሦባል፣ ፅብዖን፣ ዓና፣ ዲሶን፣ ኤጽርና ዲሳን፤ እነዚህ በኤዶም የነበረው የሴይር ልጆች፣ የሖሪውያን የነገድ አለቆች ነበሩ። የሎጣን ልጆች፦ ሖሪና ሔማም[143]፤ የሎጣንም እኅት ቲምናዕ ትባል ነበር። የሦባል ልጆች፦ ዓልዋን፣ ማኔሐት፣ ዔባል፣ ስፎና አውናም፤ የፅብዖን ልጆች፦ አያና ዓና፤ ይህ ዓና የአባቱን የፅብዖንን አህዮች ሲጠብቅ፣ የፍል ውሃ ምንጮችን[144] በምድረ በዳ ያገኘ ሰው ነው። የዓና ልጆች፦ ዲሶንና የዓና ሴት ልጅ አህሊባማ፤ የዲሶን[145] ልጆች፦ ሔምዳን፣ ኤስባን፣ ይትራንና ክራን፤ የኤጽር ልጆች፦ ቢልሐን፣ ዛዕዋንና ዓቃን፤ የዲሳን ልጆች፦ ዑፅና አራን። የሖሪውያን የነገድ አለቆች እነዚህ ነበሩ፦ ሎጣን፣ ሦባል፣ ፅብዖን፣ ዓና፣ ዲሶን፣ ኤጽርና ዲሳን፤ እነዚህ በሴይር ምድር እንደየነገዳቸው የሖሪውያን የነገድ አለቆች ነበሩ። ንጉሥ በእስራኤል ከመንገሡ በፊት፣[146] በኤዶም የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ነበሩ፦ የቢዖር ልጅ ባላቅ በኤዶም ነበር፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ይባል ነበር። ባላቅ ሲሞት፣ የባሶራው የዛራ ልጅ ኢዮባብ በምትኩ ነገሠ። ኢዮባብ ሲሞት፣ የቴማኒው ሑሳም በምትኩ ነገሠ። ሑሳም ሲሞት፣ የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ምድር ድል ያደረጋቸው የባዳድ ልጅ ሃዳድ በምትኩ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዓዊት ይባል ነበር። ሃዳድ ሲሞት፣ የመሥሬቃው ሠምላ በምትኩ ነገሠ። ሠምላ ሲሞት፣ በወንዙ[147] አጠገብ ያለው የርሆቦቱ ሳኦል በምትኩ ነገሠ። ሳኦል ሲሞት፣ የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን በምትኩ ነገሠ። የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ሲሞት፣ ሃዳር በምትኩ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ፋዑ ይባል ነበር፤ የሚስቱም ስም መሄጣብኤል ሲሆን፣ እርሷም የሜዛሃብ ልጅ መጥሬድ የወለደቻት ነበረች። ከዔሳው የተገኙት የነገድ አለቆች ስም፣ እንደየነገዳቸውና እንደየአገራቸው ይህ ነው፦ ቲምናዕ፣ ዓልዋ፣ የቴት፣ አህሊባማ፣ ኤላ፣ ፊኖን፣ ቄኔዝ፣ ቴማን፣ ሚብሳር፣ መግዲኤልና ዒራም፤ እነዚህ፣ በያዙት ምድር እንደየይዞታቸው ከኤዶም የተገኙ የነገድ አለቆች ነበሩ። ይህም ዔሳው፣ የኤዶማውያን አባት ነው። ያዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለ ወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ። እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለ ወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፤ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ[148] እጀ ጠባብም አደረገለት። ወንድሞቹም፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን ሲያዩ፣ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ እኛ ሁላችን በዕርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ በድንገት ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች ዙሪያዋን ከበው ለእኔ ነዶ ሰገዱላት።” ወንድሞቹም፣ “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት፤ ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት። እንደ ገናም ሌላ ሕልም አለመ፤ ለወንድሞቹም፣ “እነሆ፤ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው። ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ “ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በእርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው። ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው። ከዚህም በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ወደ ሴኬም አካባቢ ሄዱ፤ እስራኤልም ዮሴፍን “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ።” አለው። ዮሴፍም “ይሁን እሺ” አለው። ያዕቆብም፣ “ሄደህ ወንድሞችህም፣ መንጎቹም ደኅና መሆናቸውን አይተህ ወሬያቸውን አምጣልኝ” አለው፤ ከኬብሮንም ሸለቆ ወደ ሴኬም ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣ ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው። ሰውየውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም፣ ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ ዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው። ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ አዩት፤ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። እነርሱም እንዲህ ተባባሉ፤ “ያ ሕልም ዐላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከጒድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።” ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ እንዲህም አለ፤ “ሕይወቱ በእጃችን አትለፍ፤ የሰው ደም አታፍስሱ፤ እዚህ ምድረ በዳ፣ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ እጃችሁን አታንሡበት።” ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ ይዘውም ወደ ጒድጓድ ጣሉት፤ ጒድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር። ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎችም እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሱ፣ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሃያ ጥሬ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጒድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “ብላቴናው ጒድጓድ ውስጥ የለም፤ የት አባቴ ልሂድ?” አለ። ከዚያም የዮሴፍን እጀ ጠባብ ወሰዱ፤ አንድ ፍየልም ዐርደው እጀ ጠባቡን በደሙ ነከሩት። በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው” አሉት። እርሱም ልብሱን ዐውቆት፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው!፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቈአል” አለ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ “በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር[149] እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ። በዚህ ጊዜ፣ የምድያም[150] ነጋዴዎች ዮሴፍን፣ ወደ ግብፅ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት። በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ፣ ኤራስ ወደተባለ ዓዶሎማዊ ሰው ወረደ፤ እርሱም ዘንድ ለመኖር ቤቱ ገባ። እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ እርሷንም አግብቶ አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ዔር ተባለ። እንደ ገናም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙን አውናን አለችው። አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ አወጣችለት፤ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር። ይሁዳ የበኵር ልጁን ዔርን፣ ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። የይሁዳ የበኵር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ቀሠፈው። በዚህ ጊዜ ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደ መሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት” አለው። አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የእርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በፈጸመ ቍጥር የወንድሙንም ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወልድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስ ነበር። ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ አድራጎት ሆኖ ስለ ተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሞት ቀሠፈው። ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፣ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጒር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር፣ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጒር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች። ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ መልእክተኛው ግን ሴትየዋን ሊያገኛት አልቻለም። “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት። መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፣ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልኩም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፤ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ። ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው። ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ። እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው። ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም። የመውለጃዋ ጊዜ እንደ ደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ። በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤ ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ከዚያም ስሙ ፋሬስ[151] ተባለ። ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፣ ስሙም ዛራ[152] ተባለ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር (ያህዌ) የግብፃዊውን ቤት ባረከ፣ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፣ ማናቸውንም ጒዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቊመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፣ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጒተውም፣ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሮአል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ ለእርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።” ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው። ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።” ጌታውም “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ፣ ተቈጣ። ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፣ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፣ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለማንኛውም ጒዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር። ከዚህም በኋላ የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብፅን ንጉሥ በደሉት። ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በሁለቱም ሹማምቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው። የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር። እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደ ቈዩም፣ ታስረው የነበሩት የግብፅ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው። በማግስቱ ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት አብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው። እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጒምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቊጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።” የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች[153] በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።” ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤[154] ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤ የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው።[155] የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው። ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ እነሆ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጒምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው። በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ[156]ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ። ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጒምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። ከእነርሱም በኋላ፣ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። እንደዚሁም፣ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።” ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። “አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። የሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።” ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ[157] ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።” ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን “በመላዪቱ የግብፅ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፣ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው።[158] ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ[159]” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብፅ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው። ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱ[160] ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብፅ ምድር ተዘዋወረ። ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ። በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር። ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፣ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) መከራዬን ሁሉ፣ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ[161] አለው። እንደዚሁም፣ “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም[162] አለው። በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር። ራቡ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፣ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው። ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለሄደ፣ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር። ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ። ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ፣ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ? በግብፅ እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ከመሞት መሰንበት ይሻላልና ወደዚያው ወርዳችሁ እህል ሸምቱልን” አላቸው። ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ወረዱ። ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፣ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋር አላከውም። ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፣ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት። ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፣ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቍጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፣ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም። በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤ ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።” እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፤ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፣ አንዱ ግን የለም” አሉት። ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ! ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። በሉ፣ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፣ እስር ቤት ትቈያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፣ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው። ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው። በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ። እርስ በርሳቸውም፣ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ፣ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው። ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር። ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደ ገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው። በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጒዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣ እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጒዞአቸውን ቀጠሉ። በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ። እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፣ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቍጣ ተናገረን። እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም። እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን፣ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’ “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ። ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያንም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።” ’ እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቾቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደ ተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ። አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ ኧረ ምን ጒድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። በዚህን ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “መልሼ ባላመጣው፣ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው፤ ኀላፊነቱን ለእኔ ተውልኝ፤ እኔው መልሼ አመጣዋለሁ” አለው። ያዕቆብም፣ “ልጄ አብሮአችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቶአል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፣ ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር[163] ታወርዱታላችሁ” አላቸው። ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ ከግብፅ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው “እስቲ እንደ ገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው። ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰውዪ ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።” እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደ ገናም አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታድያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት። ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛ እኔ ልሁን። ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።” ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውዬው በቶሎ ሂዱ። ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል[164] አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።” ሰዎቹም እጅ መንሻውን፣ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብፅም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ። ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው። አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው፣ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውዬው ጥቃት ሊፈጽምብን፣ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ። ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ እንዲህም አሉት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፣ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፣ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት። የቤቱ አዛዥም፣ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ (ኤሎሂም) ነው፤ እኔ እንደሆንኩ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው። የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ። ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው። እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው’። በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት። ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይባርክህ” አለው። ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ። ፊቱን ከታጠበ በኋላ፣ ተመልሶ፣ ስሜቱን በመቈጣጠር፣ “ማእድ ይቅረብ” አለ። ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። ወንድማማቾቹ ከበኵሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜአቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፣ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ “የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ብር በየስልቻቸው አፍ ክተተው። ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋር ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። ጎሕ ሲቀድ ሰዎቹ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። ከከተማው ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፣ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ ‘እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፣ “ለበጎ ነገር ስለ ምን ክፉ መለሳችሁ? ይህ ጌታዬ የሚጠጣበት፣ የተሰወረ ነገርም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? የፈጸማችሁት ድርጊት ክፉ ነው” በላቸው። የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፣ ልክ እንደ ተባለው ተናገራቸው። እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ። ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፣ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ። ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ። ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጦአል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ። ዮሴፍም፣ “ይህንንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው። ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖን ያህል የተከበርህ ስለ ሆንህ፣ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። ጌታዬ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቈ ነበር። እኛም፣ ‘አዎን፣ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቶአል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር። “ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ አብሮአችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገርነው። “ከዚያም አባታችን ‘እስቲ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። “አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፣ “በእርግጥ የአውሬ እራት ሆኖአል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቶአል። አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጒዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር[165] ታወርዱታላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፣ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፣ የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። እኔ አገልጋይ፣ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፣ ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቍጠረኝ’ በማለት፣ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። “ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ። ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።” በዚያን ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ፣ ግብፃውያን ሰሙት፤ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ። ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለ ነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም። ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፤ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አሁንም በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም ዐትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና አሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና[166] ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። “ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብፅ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ። አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የመላው ግብፅ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። ገና ወደ ፊት የሚመጣ የአምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ ያለበለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’ “ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው። በግብፅ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ። ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው። የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መጨዋወት ጀመሩ። የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው። ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ። ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’ “ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ። ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ” የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው። ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና አምስት የክት ልብስ ሰጠው። ለአባቱም በግብፅ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት። ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከእርሱም ሲሰናበቱ፣ መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” አላቸው። እነርሱም ከግብፅ ወጥተው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ። አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብፅ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኖአል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብፅ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ። እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) መሥዋዕት ሠዋ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፣ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ነኝ፤ ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤ አብሬህ ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፤ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፤ የዮሴፍ የራሱ እጆችም ዐይኖችህን ይገጥሟቸዋል።” ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላካቸው ሠረገላዎች ላይ አወጧቸው። ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብፅ ወረዱ። ወደ ግብፅም የወረደው፣ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን ማለት ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው። ወደ ግብፅ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ ያዕቆብና ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል። የሮቤል ልጆች፦ ሄኖኅ፣ ፈሉሶ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው። የስምዖን ልጆች፦ ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው። የሌዊ ልጆች፦ ጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው። የይሁዳ ልጆች፦ ዔር፣ አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ። የይሳኮር ልጆች፦ ቶላ፣ ፉዋ፣ ዮብና ሺምሮን ናቸው፤ የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤ እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቍጥር ሠላሳ ሦስት ነው። የጋድ ልጆች፦ ጽፎን፣ ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤ የአሴር ልጆች፦ ዪምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤ የበሪዓ ልጆች፦ ሐቤርና መልኪኤል ናቸው፤ እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ፣ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤ በግብፅም የሄልዮቱ[169] ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት። የብንያም ልጆች፦ ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ናዕማን፣ አኪ፣ ሮስ፣ ማንፌን ሑፊምና አርድ ናቸው። እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። የዳን ልጅ፦ ሑሺም ነው፤ የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዬጽርና ሺሌም ናቸው፤ እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ሥልሳ ስድስት ሲሆን ይህ ቍጥር ግን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም። ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች[170] ጨምሮ፣ ወደ ግብፅ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቍጥር ሰባ ነበር። ያዕቆብም ወደ ጌሤም ለመሄድ መመሪያን ይቀበል ዘንድ፣ ይሁዳን አስቀድሞ ወደ ዮሴፍ ላከው። እነርሱም ጌሤም ሲደርሱ፣ ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደ ደረሰ፣ ዐንገቱ ላይ[172] ተጠምጥሞ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ። እስራኤልም ዮሴፍን፣ “በሕይወት መኖርህን ስላየሁ፣ ከእንግዲህ ብሞትም አይቈጨኝ” አለው። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ አናግረዋለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፣ ‘በከነዓን ምድር የሚኖሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል። ሰዎቹ ከብት የሚጠብቁ ስለሆኑ እረኞች ናቸው፤ ሲመጡም በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’ ፈርዖን አስጠርቶአችሁ፣ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ እናንተ ‘እኛ ባሮችህ ሥራችን ከልጅነታችን ጀምሮ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት ማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። ከዚያም ግብፃውያን ከብት አርቢዎችን እንደ ጸያፍ ስለሚቈጥሩ፣ በጌሤም ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።” ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው። ከወንድሞቹም መካከል አምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው። ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት፤ ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት። ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤ የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኀላፊዎች አድርጋቸው።” ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አግብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብ ፈርዖንን ከመረቀው[173] በኋላ ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው። ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍኩት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር አጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት። ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ። ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብፅ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው። ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቍጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ። በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤ ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት። ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ አለ። ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ። ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በስተቀር፣ አንዳች ነገር የለም። ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የእርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።” ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። ዮሴፍም የግብፅን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር[174] የፈርዖን ገባር አደረገው። ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ ድርጎ ስለሚያገኙና ፈርዖን ከሚሰጣቸው ድርጎ በቂ ምግብ ስለ ነበራቸው ነው፤ ከዚህም የተነሣ መሬታቸውን አልሸጡም። ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከአምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፤ ከአምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።” እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን፣ ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት። ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ አምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝ የመሬት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በዚያን ጊዜ በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት አፈሩ፤ ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር። ያዕቆብ በግብፅ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር። እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደ ተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብፅ አትቅበረኝ፤ እኔም ከአባቶቼ ጋር ሳንቀላፋ፣ ከግብፅ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦታ ቅበረኝ።” ዮሴፍም፣ “እሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለ። ያዕቆብም፣ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በዐልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጐንበስ አለ።[175] ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለ ተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቶአል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ ዐልጋው ላይ ተቀመጠ። ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ[176] በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚነሡ ዘሮችህ የዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’ “ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቈጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ። ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላቸው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቈጠራሉ። ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ መልስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፣ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ ዐዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።” እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤ ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት፤ እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ። በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው። እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና ዐያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጒልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተ ቀኝ፣ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ፣ ከእስራኤል በስተ ቀኝ በኩል አቀረባቸው። እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፤ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኵሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የተመላለሱት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ (ኤሎሂም) ከጒዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይስሐቅ ስም ይጠሩ፤ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ። ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም በኵሩ ይህኛው ስለ ሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እምቢ አለው። በዚያን ዕለት ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “በአንተ ስም እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመርቃል፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ።” በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው። ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል። እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኳትን ዐምባ ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”[177] ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን ሁሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባችሁ እነግራችሁ ዘንድ ተሰብሰቡ። “እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ ተሰብሰቡና ስሙ፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ፤ “ሮቤል፣ አንተ የበኵር ልጄ ነህ፤ ኀይሌና የጒብዝናዬም መጀመሪያ፤ በክብር ትልቃለህ በኀይልም ትበልጣለህ። እንደ ውሃ የዋለልህ ነህና እልቅና አይኖርህም፤ የአባትህን መኝታ ደፍረሃል፤ ምንጣፌንም አርክሰሃል። ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች፣ ሰይፎቻቸው[178] የዐመፅ መሣሪያዎች ናቸው። ወደ ሸንጎአቸው አልግባ፤ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፤ በቍጣ ተነሣሥተው ሰዎችን ገድለዋል፤ የበሬዎችንም ቋንጃ እንዳሻቸው ቈራርጠዋል። እጅግ አስፈሪ የሆነ ቍጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፤ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ። “ይሁዳ፣[179] ወንድሞችህ ይወድሱሃል፤ እጅህም የጠላቶችህን ዐንገት ዐንቆ ይይዛል፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይሰግዱልሃል። “አንተ የአንበሳ ደቦል ይሁዳ፤ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት አንበሳም ያደባል፤ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው እስኪመጣ ድረስ፣[180] ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል። አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጐናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል። ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ። “ዛብሎን፣ በባሕር ዳር ይኖራል፤ የመርከቦች መጠጊያም ይሆናል፤ ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል። “ይሳኮር፣ ዐጥንተ ብርቱ አህያ፣ በጭነት[181] መካከል የሚተኛ፣ ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ ትከሻውን ለሸክም ያመቻቻል፤ ተገድዶም ያገለግላል። “ዳን፣[182] ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣ በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል። ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣ የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣ የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል። “እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ)፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ። “ጋድን[183] ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል። “አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤ ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል። “ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣ የሚያማምሩም ግልገሎች[184] እንደምትወልድ ሚዳቋ ነው። ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።[185] ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤ በጥላቻም ነደፉት። ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣ እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ። አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣[187] ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል። ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትህ በረከት ይበልጣል፤[188] ይኸ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።[189] ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ይከፋፈላል። እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሶአል፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤ ይህ በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ ውስጥ ያለው ዋሻ፣ የመቃብር ቦታ እንዲሆን አብርሃም ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ ከነዕርሻ ቦታው የገዛው ነው። በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤ እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው። ዕርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን[190] ላይ ነው።” ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ፣ እግሮቹን በዐልጋው ላይ ሰብስቦ፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዮሴፍ በአባቱ ፊት ተደፍቶ አለቀሰ፣ ሳመውም። ከዚያም የአባቱ የእስራኤል ሬሳ እንዳይፈርስ ባለ መድኀኒት የሆኑ አገልጋዮቹ በመድኀኒት እንዲቀቡት አዘዘ። ባለ መድኀኒቶቹም እንዳይፈርስ ሬሳውን፣ በመድኀኒት ቀቡት። ሬሳው እንዳይፈርስ መድኀኒት መቀባቱ በአገሩ ልማድ መሠረት አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ግብፃውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት። የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩልኝ፣ ‘የምሞትበት ጊዜ ስለ ተቃረበ፣ በከነዓን ምድር ራሴ ቈፍሬ ባዘጋጀሁት መቃብር እንድትቀብረኝ’ ሲል አባቴ አስምሎኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ልቅበር ከዚያም እመለሳለሁ።” ፈርዖንም፣ “ባስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው። ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የግብፅ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት። እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ አብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ። እንዲሁም ሠረገሎችና ፈረሰኞች[191] አብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበረ። እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ልቅሶ ተቀመጠ። በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብፃውያን መራራ ልቅሶአቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል[192] ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር። የያዕቆብ ልጆችም አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አስከሬኑን ወደ ከነዓን ምድር ወስደው አብርሃም ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ላይ ከነዕርሻው በገዛው፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት። ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ፣ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር አብረውት ሄደው ከነበሩት ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ተመለሰ። የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም፣ የእኛን የአባትህን አምላክ (ኤሎሂም) አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት። ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቦታ ማን አስቀመጠኝ? እናንተ እኔን ለመጒዳት አስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦ፣ በደግ ቃል አናገራቸው። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋር በግብፅ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤ የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ። የምናሴ ልጅ ማኪር የወለዳቸውም ልጆች በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን፣ “እነሆ፤ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቦአል፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በረድኤቱ ይጐበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያን ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” ሲል አስማላቸው። ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ፤ ሬሳው እንዳይፈርስ በአገሩ ደንብ በመድኀኒት ከደረቀ በኋላ ሣጥን ውስጥ አስገብተው በግብፅ ምድር አስቀመጡት።
   ብሉይ ኪዳን    አዲስ ኪዳን   Hide Verse Numbers    Hide Chapter Numbers